Salem Magazine

Salem Magazine

Share

Celebrating 10 Years.

Salem Media (ሳሌም) is a digital and print publication that focuses on lifestyle, news, arts, and entertainment in the Ethiopian, Eritrean, and African communities in the United States.

28/08/2026

ከመጠን ያለፈ ውፍረትና ከሐኪም ማስጠንቀቂያ እስከ ሚስ ዩኤስኤ (Miss USA) መድረክ::

አምስት ዓመታት በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሆን ሕያው ምስክር ይዛ የቀረበችው የ41 ዓመቷ አሜሪካዊትና የሦስት ልጆች እናት አምበር ኡለር ናት። በ2021 ወደ 300 ፓውንድ የምትመዝን ሲሆን፣ በወቅቱ የነበራት ከባድ የጤና እክልና ከመጠን ያለፈ ውፍረት (Morbid Obesity) ሕይወቷን ለአደጋ አጋልጦት ነበር።

የሕክምና ባለሙያዎች «ቀሪ ዘመንሽን እያሳጠርሽ ነው፤ ወደ መቃብር እየተጣደፍሽ ስለሆነ አስቸኳይ ለውጥ ካላደረግሽ ልጆችሽ ከከፍተኛ ትምህርት ሲመረቁ ለማየት አትበቂም» የሚል ከባድ ማስጠንቀቂያ የለውጥ ጉዞዋን በቁርጠኝነት እንድትጀምር አደረጋት።
ይህ አጋጣሚ በሕይወቷ ውስጥ እጅግ ያፈረችበት ቢሆንም፣ የውስጥ ማንነቷን ቀስቅሶ አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምር ብርታት ሆናታል።

ጃንዋሪ 1 ቀን 2021 ዓ.ም. አምበር በግል ማስታወሻዋ ላይ አንድ ትልቅ ግብ አስፈረመች፡ «ክብደቴን ቀንሼ በቁንጅና ውድድር ላይ እሳተፋለሁ» የሚል ነበር። በወቅቱ በነበራት የአካል ቁመና ይህንን ማሰብ የማይቻል ቅዠት ይመስል ነበር። ሆኖም ግን፣ ያለ ምንም ዘመናዊ የክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች (እንደ Ozempic ያሉ)፣ በራሷ ቁርጠኝነት፣ በጠንካራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና በተስተካከለ አመጋገብ ብቻ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 170 ፓውንድ (77 ኪሎ ግራም) መቀነስ ቻለች።

አምበር ክብደቷን በመቀነስ ብቻ አላቆመችም። የነበራትን ህልም እውን ለማድረግ በመጀመሪያ በ2024 የ«ሚስስ ፍሎሪዳ ዩኒቨርስ» (Mrs. Florida Universe) አሸናፊ ሆነች። በመቀጠልም በ2025 የ«ሚስስ ዩኒቨርስ ዩኤስኤ» (Mrs. Universe USA) ዘውድን ተቀዳጀች። አሁን ላይ ደግሞ ሚቺጋን ግዛትን በመወከል በ75ኛው ሚስ ዩኤስኤ 2026 (Miss USA 2026)ታላቅ የቁንጅና ውድድር ላይ አምበር ኡለር በሁለት ታላላቅ ምክንያቶች የውድድሩን ታሪክ ቀይራለች።

በ41 ዓመቷ በውድድሩ ታሪክ ውስጥ የተሳተፈች እድሜ ጠገቧ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅታለች። (ይህ የሆነው ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን የዕድሜ ገደብ በማንሳቱ ነው)። ሌላው ደግሞ ውድድሩ ያገቡና ልጆች ያሏቸውን ሴቶች እንዲሳተፉ ከፈቀደ ወዲህ፣ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አምበር የመጀመሪያዋ እናት ለመጨረሻው ዙር ያለፈች ተወዳዳሪ አድርጓታል።

አምበር አሁን ላይ ከመድረክ ውበቷ ባሻገር፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የውኃ ውስጥ መዋኘት አደጋዎች ለመከላከል (Swim safety and drowning prevention) ጠንካራ ማኅበራዊ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች።

አምበር ኡህለር በ41 ዓመቷ የውድድሩ እድሜ ጠገብ ተወዳዳሪ በመሆን እና 170 ፓውንድ (77 ኪሎ ግራም) በመቀነስ ባሳየችው አበረታች የክብደት ለውጥ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን አግኝታለች፣ በዘንድሮው ሚስUSA
ከአሸናፊዋ በላይ መነጋገሪያ ሆናለች። አምበር ዋናውን ሚስ ዩኤስኤ የክብር ዘውድ ባታሸንፍም፣ በውድድሩ ወቅት የ”ሚስ ኮንጄኒያሊቲ” (ተወዳጅና ተግባቢ) ተብላ ዘውድ ደፍታ ሽልማትን አግኝታለች።

አምበር ኡለር ለዓለም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት አንድ ነው፡ «የሰው ልጅ የራሱን የሕይወት ታሪክ በገዛ እጁ መልሶ መጻፍ ይችላል፤ ለዚህ ደግሞ ዕድሜም ሆነ ያለፉ ውድቀቶች እንቅፋት ሊሆኑ አይችሉም።»

Daniel Gebremariam

23/08/2026

በህጻናት ጋብቻ ላይ አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት ኢማም ከጣሊያን ተባረሩ

በጣሊያን ብሬሻ ከተማ ለስድስት ዓመታት የኖሩትና የ25 ዓመቱ ወጣት ፓኪስታናዊ የሃይማኖት መሪ (ኢማም) አሊ ካሺፍ፣ የ9 ዓመት ታዳጊ ህጻናትን ከአዋቂ ወንዶች ጋር ማጋባት እንደሚቻል በምስጢር ካሜራ በተቀረጸ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በይፋ በመናገራቸው ምክንያት የጣሊያን መንግስት በአስቸኳይ ከሀገር እንዲባረሩ ማድረጉ ታወቀ።

የሀገሪቱ የደህንነትና የህዝብ ሰላም አስከባሪ አካላት እንደገለጹት፣ በብሬሽያ ከተማ ብዙ ወጣት ተከታይ ያፈሩት እና አወዛጋቢ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቀትን ይህንን ኢማም ፣ አንድ የጣሊያን የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰራ ጋዜጠኛ መሆኑን ሳያሳውቃቸው በተደበቀ ካሜራ ውይይታቸው እንዲቀረፅ በማድረግ ስለ ህፃናት ጋብቻ ላነሳላቸው ጥያቄ ኢማሙ “ሴት ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ካየች በኋላ ለአካለ መጠን ደርሳለች ማለት በመሆኑ በ9 ዓመቷ በ30ዎቹ እና በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች ጋር መጋባት ትችላለች” ብለዉ የመለሱትን መልስ ‘ፉኦሪ ዳል ኮሮ’ (Fuori dal Coro) በተሰኘው የሀገሪቱ ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እንዲተላለፍ በማድረጉ፣ በመላው ጣሊያን ከፍተኛ የህዝብ ቁጣንና ውግዘትን ቀስቅሷል።

የብሬሻ ከተማ የፖሊስ ኮሚሽነር ፓኦሎ ሳርቶሪ ባስተላለፉት አስቸኳይ ትዕዛዝ፣ የኢማሙ አስተያየት የጣሊያንን ህግ፣ የሰብአዊ መብት እሴቶችንና የህጻናትን ደህንነት የሚፃረር ከመሆኑም በላይ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ስጋት መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም ግለሰቡ በጣሊያን ለመኖር ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳልነበራቸው ተረጋግጧል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ መንግስት ለጉዳዩ ፈጣን ምላሽ በመስጠት፣ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውለው በምላሹ ወደ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ በሚበር የአየር በረራ በቁጥጥር ስር ሆነው እንዲሸኙ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ በሰጡት መግለጫ፣ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ የሀገሪቱ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስታውቀዋል፣ ከጣሊያን ህግና ማህበራዊ እሴቶች ጋር የማይጣጣሙ ባህላዊና ፅንፈኛ ልምዶችን እንደማይታገሱ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ የስደተኞች አያያዝ፣ የሃይማኖት ነፃነት እና የህጻናት መብት ጥበቃ ዙሪያ አዳዲስ ሰፊ የፖለቲካ እና የህግ ክርክሮችን ቀስቅሶ ይገኛል።

22/08/2026

ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንግሊዛዊው ደራሲና ገጣሚ ለምን ሲሳይ ሆስፒታል ገባ::

እውቁ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንግሊዛዊው ደራሲና ገጣሚ ለምን ሲሳይ ፀጉር ቤት በተቀባው የፀጉር ቀለም ምክንያት ባሳየው ከፍተኛ አለርጂ ምላሽ ምክንያት በአስቸኳይ ሆስፒታል ገብቶ የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑ ተገለፀ።

በብራድፎርድ ከተማ በሚገኝ አንድ የፀጉር ማስተካከያ ቤት ውስጥ ለምን ሲሳይ ፀጉሩን በመስተካከል በነበረበት ወቅት ፀጉር ቆራጩ “ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሮ የተሰራ የፀጉር ቀለም ነው” በማለት እንዲሞክረው ገፉፍቶ የቀባው አዲስ የፀጉር ቀለም ራሱን የሆስፒታል አልጋ ላይ እንዲያገኘው አድርጎታል።

ገጣሚው ፀጉሩን ተስተካክሎና ቀለም ተቀብት ከጨረሰ በኋላ ወደ ቤቱ በሚጓዝበት ወቅት፣ ከፍተኛ የመለብለብ እና የማሳከክ ስሜት እንደጀመረው ጠቅሷል። ከሰዓታት በኋላ ህመሙ እየተባባሰ የራስ ቅሉ፣ ሙሉ ፊቱ እና አንገቱ ላይ ከባድ እብጠት በማጋጠሙ በመጀመሪያ ወደ ፋርማሲስት ዘንድ በመሄድ ቅባትና ፀረ-አለርጂ መድኃኒቶችን ቢወስድም ሁኔታው ይበልጥ እየተባባሰ በመምጣቱ፥ በመጨረሻም ወደ ሆስፒታል ሊያመራ ችሏል።

የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት፥ ገጣሚው ከደረሰበት የኬሚካል መመረዝ ምክንያት የደረሰው ጉዳት ሙሉ በሙሉ ድኖ ለማገገም ጥቂት ወራቶችን እንደሚወስድበት ገልፀውለታል። በአሁኑ ወቅት ግን በአስተማማኝ እጅ ላይ ጥሩ የህክምና ክትትል እያገኘ እንደሆነ ታውቋል።

የህክምና ባለሙያዎች ይህንን ክስተት ተከትሎ ለህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በፀጉር ቀለሞች ውስጥ የሚገኘው PPD (Para-phenylenediamine) የተሰኘው ኬሚካል እጅግ አደገኛ የሆነ የአለርጂ ምላሽ ሊያስከትል እንደሚችል አስታውቀዋል። የጤና ዘገባዎች እንደሚያስጠነቅቁት፥ ማንኛውንም የፀጉር ቀለም ከመጠቀማችን በፊት ለ48 ሰዓታት የሚቆይ የቆዳ መሞከሪያ (Patch test) ማድረግ ግዴታ መሆን አለበት። ከዚህ ቀደም መሰል የአለርጂ ክስተቶች እስከ ህይወት ማጣት ያደረሱ የጤና እክሎችን አስከትለዋል።

ፀጉር አስተካካዩ ገጣሚውን የቀባው ቀለም ፈቃድ የሌለው ሆኖ ከተገኘ በፀጉር አስተካካዩ ላይ ፈቃድ የሌለው ምርትን በመጠቀም አደጋ ማድረስ የሚል የሙያ ቸልተኝነት ክስ ሊመሰረትበት ይችላል።

ለምን ሲሳይ በዘመናችን የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፈ ድንቅ ባለቅኔ ነው። በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ይፋዊ ገጣሚ ሆኖ በመመረጥ ታሪክ የሰራ ሲሆን፣ በልጅነቱ በእንግሊዝ የጉዲፈቻና የማህበራዊ እንክብካቤ ስርዓት (Foster care) ውስጥ ያሳለፈውን መራራና ማንነትን የማፈላለግ የህይወት ውጣ ውረድ የከተበበት “My Name Is Why” (ስሜ ለምን ይባላል) የተሰኘው የግል ማስታወሻ መጽሐፉ (Memoir) በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዛት ከተሸጡ መጻሕፍት (Best-seller) ተርታ ይሰለፋል።

ለምን ሲሳይ በተጨማሪም የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር በመሆን ያገለገለ ሲሆን፥ ለስነ-ጽሁፍ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ ከእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብ የላቀ የክብር ማዕረግን ተቀብሏል።

በአሁኑ ሰዓት ከመላው ዓለም የተውጣጡ አድናቂዎቹ፣ ደራሲያን እና የጥበብ ወዳጆች ፈጣን ማገገምን እየተመኙለት ይገኛሉ።

Daniel Gebremariam

22/08/2026

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጠቅለያዎቹ ላይ የሚያሰፍረው የአሜሪካው በርገር ቤት

በአሜሪካ አገር 424 ቅርንጫፎች ያሉት እና ከ28,000 በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው ዝነኛው የፈጣን ምግብ ሰንሰለት ኢን-ኤንድ-አውት (In-N-Out Burger) በሚሸጣቸው የበርገር ማሸጊያዎች ላይ የሚያትማቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በደንበኞች እና በሲቪል መብት ተሟጋቾች መካከል ሰፊ የሃሳብ መከፋፈል ፈጥረዋል።

ተቋሙ በለስላሳ መጠጥ መያዣ እቃዎች የታችኛው ክፍል እና በበርገር መጠቅለያ ወረቀቶች ላይ እንደ “ዮሐንስ 3:16”፣ “ምሳሌ 3:5”፣ “ምሳሌ 24:16”፣ “ናሆም 1:7”፣ “ሉቃስ 6:35” እና “ራዕይ 3:20” የመሳሰሉ ጥቅሶችን የሚያትምባቸው ሲሆን፣ ይህም አሰራር የተጀመረው ከ46 ዓመት በፊት በድርጅቱ መስራች በነበሩት ሐሪ ስናይደር አማካኝነት የቤተሰቡን የክርስትና እምነት ለማንጸባረቅ ታስቦ ነበር።

የድርጅቱ ደጋፊዎች ማናቸውም የግል ኩባንያ በራሱ ምርት ላይ የፈለገውን ነገር የማድረግ ሙሉ መብት እንዳለውና ጥቅሶቹም ማንንም ደንበኛ እምነት እንዲቀይር እንደማያስገድዱ ይከራከራሉ።

በአንጻሩ ነቃፊዎች ደግሞ ተቋሙ የተለያየ እምነት ያላቸውንና ምንም እምነት የሌላቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የሚያስተናግድ አገር አቀፍ የንግድ ሰንሰለት በመሆኑ፣ የበርገር መጠቅለያ ወይም የፈሳሽ መያዣ የወረቀት ብርጭቆዎች ላይ የሃይማኖት መልዕክቶች ፈጽሞ መኖር የለባቸውም ሲሉ ይተቻሉ።

የአሁኗ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የመስራቹ የልጅ ልጅ የሆኑት ሊንሲ ስናይደር ይህንን ተግባር እንደ ቤተሰብ መዘከሪያ ቅርስ በመቁጠር ከአቋማቸው ፍንክች እንደማይሉ በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፣ በጥቅሶቹ ምክንያት ነቀፌታ እና የተሟጋቾች ግፊት ቢኖርም የኩባንያው ቅርንጫፎች መስፋፋታቸውን እና የድርጅቱ ተወዳጅነት ከመጨመር ወደ ኋላ አላለም።

21/08/2026

በአሰቃቂ የተኩስ አደጋ የጓደኛውን ሕይወት ያጠፋው የ12 ዓመት ታዳጊ ፍርድ ቤት ቀረበ

በዋሽንግተን ዲሲ የ13 ዓመቱን ታዳጊ አህመድ ሚምስን በሽጉጥ ተኩሶ በመግደል ነፍስ በማጥፋት ወንጀል የተከሰሰው የ12 ዓመት ታዳጊ ሐሙስ ዕለት በዲሲ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

በችሎቱ ሂደት ላይ ታዳጊው ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ያለቀሰ ሲሆን፣ እናቱ ከፍርድ ቤቱ ውጭ ሆና በቪዲዮ መገናኛ አማካኝነት ሂደቱን በከፍተኛ ሐዘን ስትከታተል ተስተውላለች።

በታዳጊው ላይ የጦር መሣሪያ ካለፈቃድ መታጠቅ ፣ የሰውን ህይወት በቸልተኝነት ማጥፋት እንዲሁም ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ይዞታ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።

የዋሺንግተን ዲሲ ፖሊስ መምሪያ (MPD) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ አሳዛኙ የተኩስ አደጋ የተፈጸመው ባለፈው አገስት 11 ቀን በሰሜን ምስራቅ ዋሽንግተን 1600 ሮዝዴል ስትሪት (1600 block of Rosedale Street, NE) በተባለ አካባቢ ነው።

ከተጠርጣሪው ታዳጊ የተገኘው የቃል ምስክርነት እንደሚያመለክተው፣ ጓደኛው ከእርሱ ጋር ለመጫወት አዘውትሮ እንደሚያደርገው ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንደመጣና አብረው መጫወት እንደጀመሩ ገልፆ፣ በጨዋታቸው መሀከል የወንድሙ ሽጉጥ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ እንደተመለከተ እና ሽጉጡን አንስቶ እየፎከረና እየዘለለ በነበረበት ወቅት ሸጉጡ በድንገት ባርቆ ጓደኛውን እንደገደለው አመልክቷል።

መሣሪያው ተኩሶ የአህመድን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ታዳጊው በከፍተኛ ድንጋጤ በመዋጥ የአህመድን አስከሬን ከቤት ውስጥ ጎትቶ በማውጣት በሕዝብ መሄጃ እግረኛ መንገድ ላይ እንደጣለው አምኗል።ከአደጋው ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ታዳጊው እና ቤተሰቡ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ መምሪያ በመሄድ እጃቸውን ሰጥተዋል።

ፖሊስ እንደገለጸው፣ ቤተሰቡ ስለ ክስተቱ ሦስት የተለያዩ የእምነት ቃል መግለጫዎችን የሰጡ ሲሆን፣ በመጨረሻም ድርጊቱ ድንገተኛ አደጋ መሆኑን በሚገልጸው ሦስተኛው መግለጫ ላይ ጸንተዋል። ባለሥልጣናት ይህንን ሦስተኛ የቃል ምስክርነት የተቀበሉት ሲሆን፣ ሕፃኑም እውነታው እርሱ መሆኑን ለመርማሪዎች አረጋግጧል።

የአህመድ ሚምስ አያት ወይዘሮ ሞኒካ ሚምስ የልጅ ልጃቸውን ሲያስታውሱ፣ “ውጭ መውጣትን እና ከጓደኞቹ ጋር መጫወትን የሚወድ በጣም የዋህ እና ቅን ልጅ ነበር” ብለዋል። አያት አክለውም፣ “ይህ በእርሱ ላይ በመፈጸሙ እጅግ ደንግጫለሁ፣ ተጎድቻለሁም። በጣም ደግ ልጅ ነበር፤ ሌሎችን መርዳት ይወድ ነበር። በእውነት መልካም ልጅ ነው፤ በፍጹም ረብሻ ውስጥ የሚገኝ አይነት ልጅ አልነበረም” ሲሉ በሐዘን ገልጸዋል።

የዲሲ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተባባሪ ዳኛ ስቲቨን ዌልነር የ12 ዓመቱ ታዳጊ ለሕብረተሰቡ ደህንነት አስጊ ነው ሲሉ በሰጡት ውሳኔ፣ ታዳጊው በዲሲ የወጣቶች እስር ቤት ማእከል ዉስጥ በቁጥጥር ስር ውሎ እንዲቆይ አዘዋል። በተጨማሪም በሚቀጥለው ሳምንት ለሚኖረው የፍርድ ቤት ችሎት እስኪቀርብ ድረስ የአእምሮ ጤና ምርመራ እንዲደረግለት ዳኛው ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

Daniel Gebremariam

20/08/2026

የደቡብ ኮሪያ ጠንቋዮች AI ገብያችንን ክፋኛ ቀንሶብናል ብለው አማረሩ።

በቴክኖሎጂ ምጥቀት ቀዳሚ ከሆኑት የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ደቡብ ኮሪያ፣ የቅርብ ጊዜው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዕድገት የዘመናት ታሪክ ባለው የባህላዊ ዕድል ትንበያ (ጥንቆላ) ኢንደስትሪ ላይ ከፍተኛ አደጋ እየደቀነ መሆኑ ተሰማ።

በአገሪቱ የሚገኙ ታዋቂ ዕድል ተንባዮችና ጠንቋዮች ወደ እነርሱ ይመጡ የነበሩ ደንበኞቻቸው ፊታቸውን ወደ AI ቴክኖሎጂ በማዞራቸው ምክንያት ሥራቸው ክፉኛ እንደ ተቀዛቀዘባቸው በምሬት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በዋና ከተማዋ ሴኡል ዳርቻ በሚገኘውና በባህላዊ ዕድል ተንባዮች (ጠንቋዮች) መንደርነቱ በሚታወቀው ‘ሚያ መንደር’ ውስጥ አሁን ላይ የደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

ቀደም ባሉ ዓመታት የደቡብ ኮሪያ ነዋሪዎች ስለ ጤናቸው፣ ትዳር፣ ፍቅር፣ ገንዘብ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ለመጠየቅ ወደዚህ መንደር በብዛት ይጎርፉ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ አብዛኞቹ ዜጎች በአካል ወደ መንደሩ ከመሄድ ይልቅ በኢንተርኔት አማካኝነት እንደ ChatGPT እና Gemini ያሉ የ-AI መተግበሪያዎችን በመጠቀም ዕድላቸውን መተንበይ መምረጣቸው ተገልጿል።

በዚሁ መንደር ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ዕድል ተንባዮች መካከል አንዷ የሆኑት የ86 ዓመቷ አዛውንት ሶንግ ኦ-ሱን ሁኔታውን ሲያስረዱ፣ እሳቸው አሁንም ከዘመናዊው የኢንተርኔት ዓለም ርቀው እንደሚኖሩና ዕድልን ለመተንበይ “አራቱ የዕጣ ፈንታ ምሰሶዎች” (Saju) የሚባለውን የኮሪያ ጥንታዊ ኮከብ ቆጠራ ዘዴ በብሬይል መጽሐፍ እያነበቡ እንደሚጠነቁሉ ገልጸዋል።

አዛውንቷ ባለፉት 40 ዓመታት ያካበቱት ይህ የሰዎች ስነ-ልቦና የመረዳትና የማማከር ልምድ AI በቀላሉ ሊተካው የማይችለው የላቀ ሰብአዊ ችሎታ መሆኑን በጽኑ ያምናሉ። “በሕይወት የመኖር ተስፋ ቆርጠው ለመሞት እንኳ ወደ እኔ የመጡ ሰዎችን አሳምኜና አጽናንቼ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ አድርጌያለሁ” ሲሉም የሥራቸውን ማኅበራዊ ፋይዳ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ የኢኮኖሚው እውነታ ሌላ ሆኗል። ቀደም ሲል በአካባቢው ከ 70 እስከ 80 የሚደርሱ ጠንቋዮች በሥራ ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ቁጥራቸው ከ20 በታች ዝቅ ብሏል። እንደ ‘ኢንኖፎሬስት’ (Innoforest) የተባለው የደቡብ ኮሪያ የጀማሪ ኩባንያዎች ትንተና ድርጅት መረጃ መሠረት፣ በአገሪቱ ያለው የዕድል ትንበያ ገበያ እጅግ ግዙፍና በ 2024 ብቻ በግምት 986 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የደረሰ ቢሆንም፣ አብዛኛው የገበያ ድርሻ ግን ወደ ዘመናዊ መተግበሪያዎች እየተዛወረ ነው።

ለዚህ ሽግግር ዋነኛው ምክንያት የዋጋና የቅልጥፍና ጉዳይ መሆኑ ይነገራል። የ-AI መተግበሪያዎች አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በነጻ ወይም በጣም በዝቅተኛ ክፍያ በሰከንዶች ውስጥ የሚሰጡ ሲሆን፣ በአንጻሩ እንደ ወይዘሮ ሶንግ ያሉ ባህላዊ ባለሙያዎች ለአንድ የዕድል ትንበያ ክፍለ-ጊዜ እስከ 35 ዶላር ገደማ ያስከፍላሉ። ይህ የዋጋ ልዩነትና የቴክኖሎጂው ተደራሽነት፣ ወጣቱ የኮሪያ ትውልድ ከባህላዊው መንደር ይልቅ ስማርት ፎኑን እንዲመርጥ ማድረጉን የዘርፉ ታዛቢዎች ገልጸዋል።

45% - 55% የሚጠጉ ደቡብ ኮርያውያን በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ የህይወት እጣ ፋንታቸው እንዲተነበይላቸው በመፈለግ ወደ ዕድል ተንባዮች (ጠንቋዮች) ቤት ያመራሉ።

Daniel Gebremariam

19/08/2026

✨ 🇪🇹 የኢትዮጵያ አዲስ አመት ክብረበዓል ከሞንጎምሪ ኮሌጅ 🇪🇹 ✨

We would love for you to join us as we celebrate the Ethiopian New Year with a wonderful day of culture, community, and connection! Bring your family and friends to experience rich traditions while exploring incredible educational and career pathways.

📅 Saturday, August 29, 2026
⏰ 11:00 a.m. – 3:00 p.m.
📍 Montgomery College

What to Expect:
🎶 Live Ethiopian cultural music and entertainment
🛍️ Ethiopian cultural vendors and artisan markets
☕ Traditional Ethiopian coffee ceremony
🤝 Community resource tables and cultural exhibits
🎉 Family-friendly activities and opportunities to connect and network
📚 Montgomery College Workforce Development and Continuing Education (WDCE) and EOC information tables

Whether you are reconnecting with your culture, discovering something new, or exploring educational and workforce opportunities at Montgomery College, there will be something for everyone! 💛💚❤️

👇 Tag a friend in the comments who needs to come with you!

Montgomery College

18/08/2026

ኢትዮጵያዊቷ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የህክምና ዶክተር ::

ታዋቂዋ የህክምና ባለሙያ፣ የህዝብ ጤና ኤክስፐርት እና ሞዴል ዶ/ር ምስክር ካሳሁን ተካ (ሚካ) በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ታዋቂው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ (Johns Hopkins University) በሕዝብ ጤና አጠባበቅ (Public Health) ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በስኬት ካጠናቀቁ በኋላ- በሞያቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በሙያቸው አጠቃላይ የሕክምና ሐኪም (General Practitioner) የሆኑት ዶ/ር ምስክር፣ እ.ኤ.አ በ2020 ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በሕክምና ሳይንስ የተመረቁ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሕክምናውና በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ በርካታ አበረታች ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

ዶ/ር ምስክር የጤና እኩልነትን (Health Equity) ማረጋገጥ፣ የአእምሮ ጤና ግንዛቤን ማሳደግ እና የጤና ፖሊሲና አስተዳደርን ማሻሻል ላይ በትኩረት እየሰሩ ያሉ ባለሙያ ናቸው። ከህክምና ስራቸው ባሻገር፣ ማህበራዊ ፈተናዎችን በበጎ ፈቃደኝነት ለመፍታት የሚያልመውን “GIV Society Ethiopia” የተሰኘ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅትን በግንባር ቀደምትነት መስርተዋል። በድርጅቱ ውስጥ በዋና ስራ አስፈፃሚነት በቆዩባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ፣ ከ800 በላይ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር ከ3,000 በላይ ለሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አስችለዋል።

ዶ/ር ምስክር በህክምና ሙያቸው ብቻ ሳይሆን በሞዴሊንግ ዘርፍም የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠሩ ስኬታማ ሴት ናቸው። በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውበት ውድድሮች ላይ ሀገራቸውን ወክለው የተሳተፉ ሲሆን፣

ከነዚህም መካከል፦
- የሚስ ሱፕራናሽናል ኢትዮጵያ 2016 አሸናፊ፣
- የሚስ ዩኒቨርስ ኢትዮጵያ 2017 አንደኛ ረዳት (1st Runner Up)፣
- የሚስ አፍሪካ ቢውቲ ክዊን 2018 የዘውድ ባለቤት መሆን ችለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በርከት ባሉ አለም አቀፍ የውበት እና የፋሽን ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፈዋል።
እነዚህን ታዋቂ መድረኮች የተጠቀሙት ዘውድ ለመድፋት ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶች ከአካዳሚክ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በኪነጥበብ እና በተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች ላይ እንዲሳተፉ እንዲሁም ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤያቸው ወጥተው ራሳቸውን እንዲያበቁ ለማስተማር እንደሆነ ይናገራሉ።

የዶ/ር ምስክር ዋና ግብ ጠንካራ የጤና አመራር (Healthcare Leadership) እና የጤና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ የኢትዮጵያንና በአጠቃላይ የአፍሪካን ማህበረሰብ የተሻለ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ለዚህም ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በዓለም አቀፍ መጽሔቶች እና በተለያዩ የፓናል ውይይቶች ላይ በመቅረብ ስለ አእምሮ ጤና፣ ሕዝብ ጤና እና ስለ ወጣቶች ሙያዊ እድገት ጠንካራ የአደባባይ ጥብቅና (Advocacy) ስራዎችን አከናውነዋል። በተጨማሪም በ “Ensight Global Consultancy” በኩል አዳዲስ የሕዝብ ጤና መፍትሄዎችን በማፍለቅ ላይ ትገኛለች።

ይህች በሙያዋ፣ በበጎ አድራጎት ስራዋ እና በኪነጥበብ ዘርፍ ደምቃ የወጣች ወጣት ዶክተር፣ የወደፊት ጉዞዋን እና የምታበረክታቸውን አገልግሎቶች በይፋዊ ድረ-ገጿ (www.miskerkassahun.com) ላይ መመልከት ይችላሉ።

Salem Magazine Salem Magazine Misker Kassahun

17/08/2026

በእንግሊዝ ሐገር ፣ በሎንዶን ከተማ አረጋዊውን አስገድዶየደፈረው የ33 ዓመቱ ኤርትራዊ ስደተኛ ጥፋተኛ ተባለ

በሰሜን ምዕራብ ሎንዶን ሃሮው በሚገኝ የአንድ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድን አረጋዊ ሰው አስገድዶ የደፈረው የ33 ዓመቱ ኤርትራዊ ስደተኛ ብሩክ ደሳለኝ በጥፋተኝነት መፈረዱን የሃሮው ክራውን ፍርድ ቤት አስታወቀ።

እንደ አቃቤ ህግ ማስረጃ እና የክስ መግለጫ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ባለፈው ዓመት ሐምሌ 23 ቀን እኩለ ሌሊት ላይ ነበር። ተከሳሹ ብሩክ ደሳለኝ በወቅቱ ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ሰክረውበቤተክርስቲያኑ አቅራቢያ በሚገኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩትንና ለህግ ጥበቃ ሲባል ስማቸው ያልተጠቀሰውን እድሜያቸው በ 60ዎቹ አጋማሽ የሆኑንአረጋዊ ጡረተኛበጉልበት በመጎተት ከወንበሩ ላይ አውርዷቸዋል። በመቀጠልም በቅድስት ዮሐንስ (St John’s) ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ወደሚገኝ ሳርማ ምድር እና የግንባታ ማገጃ በስተጀርባ በመውሰድ ለ20 ደቂቃዎች የቆየ አሰቃቂ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ፈጽሞባቸዋል።

ጥቃቱ እየተፈጸመ በነበረበት ወቅት በአቅራቢያው በሚገኝ የመኖሪያ ቤት መስኮት ላይ የነበረች አንዲት ምስክር ድርጊቱን ተመልክታ ለፖሊስ ጥሪ በማድረጓ የወንጀል መከላከል ክፍሎች በፍጥነት ወደ ስፍራው ሊደርሱ ችለዋል።

የአካባቢው ማዘጋጃ ቤት የቪዲዮ ክትትል (CCTV) ካሜራ እንደሚያሳየው፣ ተከሳሹ ጥቃቱን በሚፈጽምበት ወቅት በርካታ መኪኖች እና ባለ ሁለት ፎቅ አውቶብሶች በአቅራቢያው ያልፉ የነበረ ሲሆን፣ መንገደኞች በሚያልፉበት ቅጽበት ሁሉ ተከሳሹ ጥቃቱን ያቆም እንደነበር ተገልጿል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ ባደረገው የምርመራ ቃለ-መጠይቅ፣ ተከሳሹ በአስተርጓሚ ታግዞ በሰጠው መግለጫ “አረጋዊው ሰክረው ስለነበር ልረዳቸው እየሞከርኩ ነበር” በማለት ክዶ ነበር። ሆኖም የምርመራ መኮንኖች የማዘጋጃ ቤቱን የቪዲዮ ማስረጃ ሲያሳዩት ቃለ-መጠይቁን አቋርጦ ከአማካሪ ጠበቃው ጋር ከተነጋገረ በኋላ ተጨማሪ ቃል ከመስጠት ተቆጥቧል።

የተከሳሹ ጠበቃ ቢቢ ኢሁኦማህ ለዳኞች በሰጡት መከላከያ ድርጊቱ ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ የለም በማለት ዳኞች ስሜታዊ ውሳኔ እንዳይሰጡ ቢከራከሩም፣ ዳኞች ግን የቀረበውን የቪዲዮ እና የዓይን ምስክሮች መነሻ በማድረግ ተከሳሹን ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ ነው ብለውታል።

ተከሳሹ ብሩክ ደሳለኝ የወንጀል ቪዲዮው በፍርድ ቤት ሲታይ ምንም ዓይነት የጸጸት ስሜት ሳያሳይ በዝምታ ውሃ ሲጠጣ እንደነበር ተገልጿል።

የመርማሪው መኮንን ሉክ ሬቪል ከውሳኔው በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ “ብሩክ ደሳለኝ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አቅመ-ደካማ አረጋዊን ያጠቃ አደገኛ ወንጀለኛ ነው።
ለፖሊስ ጥቆማ የሰጡ የህዝብ አካላትን እናመሰግናለን፤ መሰል የጾታ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖች ሁሉ ወደ ፖሊስ ቀርበው እንዲያመለክቱ እናበረታታለን፣ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረግላቸዋል” ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ የሚያስተላልፈውን የቅጣት ውሳኔ በቀጣይ ቀጠሮ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

Meznagnia / መዝናኛ

17/08/2026

ታዋቂዋ አሜሪካዊት ተዋናይ ሃይደን ፓኔቲየር በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች::

ኒው ዮርክ — በአለም አቀፍ ደረጃ በቴሌቪዥን ድራማዎች እና በሆሊውድ ፊልሞች የምትታወቀው አሜሪካዊቷ ተዋናይት ሄይደን ፓኔቲየር በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ተረጋገጠ።

እሁድ ነሐሴ 16 ቀን 2026 ዓ.ም የኪነጥበብ ባለሙያዋ ተወካዮች እና ቤተሰቦቿ ለኤቢሲ ኒውስ እንደገለጹት ተዋናይቷ በድንገት ህይወቷ ማለፉን ገልፀዋል፡።

የተዋናይቷ አባት ስኪፕ ፓኔቲየር በሰጡት ልብ የሚነካ መግለጫ “ሄይደን በህይወታችን ውስጥ ትልቅ ብርሃን እና የጥንካሬ ምንጭ ነበረች፤ ለምናውቃት ሁሉ የማይለካ ፍቅርና ደስታን ያበረከተች ድንቅ ሰው ነበረች” ሲሉ በከባድ ሀዘን ገልጸዋታል። እስካሁን ድረስ ተዋናይቷ የሞቷ መንስኤ ምን እንደሆነበይፋ አልተገለጸም። ቤተሰቦቿ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የግል ነጻነታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

ሄይደን ፓኔቲየር ገና በልጅነቷ “ዋን ላይፍ ቱ ሊቭ” (One Life to Live) እና “ጋይዲንግ ላይት” (Guiding Light) በተሰኙ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልሞች ላይ በመተወን የጥበብ ጉዞዋን የጀመረች ሲሆን፣ በኋላም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተመልካቾች ዘንድ እንድትታወቅ እና እንድትወደድ ባደረጓት በርከት ያሉ ታላላቅ ፊልሞች ላይ በብቃትተውናለች።

በፌብሩዋሪ 2023 ታናሽ ወንድሟ ጃሰን ፓኔቲየር በተመሳሳይ በወጣትነቱ በ28 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል። ጃሰንም እንደ እህቱ ተዋናይ እና ስዕል ሰዓሊ ነበረ። ሄይደን ከወንድሟ ጋር የነበራት ትስስር በጣም ጥብቅ በመሆኑ፣ የእሱ መሞት ህይወቷን ሙሉ በሙሉ ያናጋ እና ክፉኛ የሰበራት ክስተት ነበር። ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ባሳተመችው “This Is Me: A Reckoning” በተሰኘው የግል ማስታወሻ መጽሐፏ ላይ፣ የወንድሟ ሞት ያደረሰባትን ስብራት እና ከዚያ በኋላ ያሳለፈችውን ከባድ የሃዘን ወቅት በግልጽ አስፍራው ነበር።

ተዋናይቷ ሄይደን ፓኔቲየር በኪነጥበብ ስኬቷ ብቻ ሳይሆን፣ በግል ህይወቷ ያጋጠሟትን ከባድ ፈተናዎች በግልጽ ለሕዝብ በማካፈልና ሌሎች ሰዎችን ከእርሷ ስህተት እንዲማሩ በምታደርገው ጥረት ትታወቃለች። በተለይ ከአዕምሮ ጤናና አሱሰኝነት ጋር አጋጥሟት የነበረዉን ችግር በይፋ ተናግራለች::

የአልኮል እና የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ እንደነበረች እና ይህም በጤናዋና በጉበቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባት እንደነበረ ፣ ከዛም ከዓመታት ተጋድሎ በኋላ ሱሱን ሙሉ በሙሉ አሸንፋ መላቀቅ ችላ እንደነበር መፅሐፏ ላይ አስፍራለች ።

ተዋናይት ሄይደን ፓኔቲየር ካያ የተባለች የአንድ የ11 ዓመት ሴት ልጅ እናት ነበረች።

Daniel Gebremariam

Telephone

Address


50 S Pickett Street
Addis Ababa
22304

Opening Hours

Monday 09:00 - 17:00
Tuesday 09:00 - 17:00
Wednesday 09:00 - 17:00
Thursday 09:00 - 17:00
Friday 09:00 - 17:00
Saturday 09:00 - 17:00
Sunday 09:00 - 17:00